የቤተክርስቲያኒቱ አመሰራረት


በሮቸሰተር ኒው ዮርክ፡ የመንክር ሀይላ ቅድስት 

ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን አመሰራረት

ቅድስት ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን፡ እግዚአብሔር ልባቸውን ባነሳሳቸው ጥቂት ምዕመናን፡ በአውሮፕያውያን ቀን አቆጣጠር ጃንዋሪ 17, 1999 (January 17, 1999) ተመሰረተ።ለዚህም መነሻው: እንደ አጋጣሚ ሆኖ የ1998 የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አመታዊ ፒክኒክ: የፍልሰታ ጾም ፊቺ ጋር ስለተገጣጠመና: በአንዳንድ እናቶች: አገራችን ብንሆን ኖሮ ዛሬ አስቀድሰን ጾም እንፈታ ነበር ሲሉ: ሌሎችም ታዲያ ለምን እዚህ ቤተክርስቲያን አይኖረንም? የሚለው የተቀደሰ ሀሳብ ስለመጣላቸው: በተለያየ ጊዜና አካባቢ እየተገናኙ ሲወያዩ ቆይተው: በጃንዋሪ 17, 1999 ላይ በነበረው ምልዐተ ጉባኤው ላይ: ለውይይት የቀረበውን ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብና ኮድ ኦፍ ኤቲክስ አጽድቆ: ስሙንም ኪደነምህረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብሎ: ቀጥሎም የሚመሩትን የቦርድ አባላት መርጦ በደስታ ተበተነ።

በወቅቱም በምዕራባውያን ሀገራት: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክስቲያናት አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ የነበሩትን: ብጹዕ አቡነ ይስሀቅን አነጋግረን: መመሪያም ተቀብለን: ብጹዕነታቸውም: ከኒው ዮርክ ሲቲ: ከኒው ጀርሲና ከቦስተን: በመሪ ጌታ አፈወርቅ የሚመራ: የቤተክርስትያን ልዑካንን ልከውልን: የመጀመሪያውን የጸሎት የዝማሬና የወንጌል ትምህርትን: በኦርቶዶክሳዊ አስተምሮ አከናውነን። በዕለቱ የቅርብ ጊዜ ዕቅድ አውጥተን: በደስታ ተለያየን።

በታቀደውም ዕቅድ መሰረት: ፌብሯሪ 23, 1999 ( February  23, 1999) ብጹዕ አቡነ ይስሀቅ በቦታው ተገኝተው: ቤተክርስቲያኑን ባርከው ከፈቱልን። በጊዜው ከብጹዕ አባታችን ጋር: የቦስተን ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አባ ሀጎስ: መሪጌታ አፈወርቅ ከጃምይካዊ መዘምራን ጋር: በተጨማሪም: ምዕመናን ከቦስተን ቅዱስ ሚካኤል: ከኒው ዮርክ ሲቲ ቅድስት ጽዮን ማርያም: ከኒው ጀርሲ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያናት: መጥተወ በቦታው በመገኘት: ትልቅ መንፈሳዊ: የጸሎት የዝማሬና የትምህርት አገልግሎት: ተሳትፈን ሁሉም በታላቅ ደስታ ወደየመጣንበት ተመልሰናል።

በወቅቱ ይህን አገልግሎት ያካሄድነው: በ3ኛ ፕረስፕተርያን (3rd Presbyterian Church on 4 Meigs St)ቤተክርስቲያን ውስጥ ነበር። ቀጥሎም: ለ9 ዓመት ያህል ያለምንም ክፍያ: በየሳምንቱ ቅዳሜ ጠዋት: ይህ ቤተክርስቲያን: ለቅድስት ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን መዕመናን: መገልገያ ቦታ ሆኖ ኖሯል። ይህን ዛሬ የምንገለገልበትን ቤተክርስቲያን: ስናገኝና ወደዚህ ስንመጣ: የፕረስፕተርያን ካህኑ: ከኛ ጋር በእግሩ ተጉዞ: እዚህ ድረስ ሸኝቶናል። መቼም የማንረሳው: ትልቅ ክርስቲያናዊ ፍቅር ያሳዩን: ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ከልብ እናመሰግናልን።

ወደቀደመው ታሪካችን እንመለስና: ታቦተ ህጉን ቀሲስ መዝገቡ ከኒው ዮርክ ሲቲ ይዘውልን መጡ። የመጀመሪያው ካህናችን አባ ገብረድንግል: ብጹዕ አቡነ ይስሀቅ ልከውልን: ከዚሁ አብሮን የነበረው ወንድማችን: በድቁና ሲያገለግል የነበረ በመሆኑ: በዚሁ ዲያቆን ሆኖ እንዲያገለግል አዘውት ስለነበር: ዲያቆን ብርሃኔ ወልደሰማያት የመጀመሪያ ዲያቆናችን ሆኖ: እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት: ሙሉ ቅዳሴ: የቁርባርንና የወንጌል አገልግሎቱ ተጀመረ።ከዚህም ቀጥሎ: የተለያዩ ካህናት መጥተው አገልግለውናል። ለሁሉም እግዚአብሔር ይስጥልን እንላለን።

 ቅድስት ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን: በአካባቢው የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስለሆነች: በባፋሎና በሲራኪዩስ ያሉ: እህት ወንድሞቻችን: ባሉበት አገልግሎት ያገኙ ዘንድ: በወቅቱ ከነበሩ ካህናችን ጋር: በመመካከርና በመስማማት: አስተዋጽኦ አድርጋለች።  በተጨማሪም: በዚህ የሚያድጉት ህጻናት: የሚያጋጥማቸውን ፈተና እና ተግዳሮት በመረዳት: አስቀድሞ በመንፈሳዊ ትምህርት: በግብረገብ: በጥበብና በባህል: እንዲኮቶኮቱ ብዙ ጥራለች። ወደፊትም በተደራጀ መልኩ: ከሌሎች ጋር በመተባበር ጥረቱ ይቀጥላል።

 ከጃንዋሪ 2008 ዓም ጀምሮ: የቀድሞው ቆሞስ አባ ሀረገወይን: የአሁኑ ብጹዕ አብነ ባስልዮስ: የዚች ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ እና: የቅዱስ ሲኖዶስ አባል: እስካሁን ድረስ: ለ14 አመት እያገለገሉን: እየባረኩን: አብረውን አሉ። ለዚህ በጣም ከፍ ያለ አክብሮት አለን። ብጹዕነታቸው ከመጡ ብዙም ሳንቆይ: ይህን ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር $400 ሺ የሚገመተውን ቤት በ$13 ሺ ብር ሰጥቶናል። ለመጀመሪያ ጊዜ: እዚሁ ተወልደው ካደጉት ልጆቻችን: ዲያቆናትን አስተምረው ክህነት ሰጥተው: ለአገልግሎት አብቅተዋል። ቀጥሎም ሌሎች ወጣት ልጆችን: ወላጆቻቸው ለዚህ የተቀደሰ ስራ ስላበረቷቷቸው: እንዲሁ አስተምረው ክህነት ሰጥተው: ለአግልግሎት አብቅተዋል። ሌላም ብዙ ስራዎችን ሰርተዋል። ለዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ሙሉ ጤንነታቸውንና እረዥም እድሜ ይሰጥልን ዘንድ: ታላቅ ምኞታችን ነው።

 በ2020 ዓም: መላከኃይል ቆሞስ አባ ወልደሩፋኤል ከመጡ ጀምሮ: ምዕመናን በማነቃቃት በማበረታታትና አብሮም በመስራት: ቤተክርስቲያችን ሙሉ ዕደሳ እንዲደረግና: ዛሬ በዚህ ተገኝታችሁ አብረን እግዚአብሄርን እንድናመሰግን: ያበቁን አባት ናቸው። ለዚህ በጣም እናመሰግናቸዋለን። ራዕያቸው ብዙ ስለሆነ: ከእግዚአብሔር ጋር ወደፊትም አብረን ብዙ ስራ እንደምንሰራ ተስፋ አለን። በዚህ ስራ ውስጥ ምዕመና የታዘብነው ነገር ቢኖር: በአባ ወልደሩፋኤል አነሳሽነት: "ማድረግ እንቸላለን" (We Can Do It!) የሚለው መንፈስ በሁላችን ላይ ሰፍኖ: ከዚህ በፊት አድርገን የማናውቀውን ስራ ሁሉ: ጉግል ሰርች (google search)እያደረግን በመስራታችን: ለቤተክርስቲያ ወጭ ከመቀነስ በተጨማሪ: የራሰችንንም ኢትዮጵያዊነት መንፈስ: ስራን ወዳድነት: የማናውቀውን ለማወቅ ዝግጁነት: ከፍ አድርገን: በተግባር አሳይተናል። በዚህም መንፈሳችን በጣም ዕረክቷል።

 ይህን ሁሉ ፈቅዶ ያከናወነልን: የልዑል እግዚአብሄር ስም ዘወትር የተመሰገነ ይሁን!!!

የእግዚአብሔር ቸርነት: የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን!!!

አባቶቻችንን በጤና በፍቅር ይጠብቅልን!!!

ሀገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክልን። ይጠብቅልን። ህዝቧንም እግዚአብሄር: በምህረቱ በቸርነቱ: በሰላም በፍቅር: በአንድነት በመከባበር ያኑርልን።

ለአለም ሁሉ ሰላምን ይስጥልን።