መልዕክቶች

ብጹዕ አቡነ ባስልዮስ መልዕክት

ብጹዕ አቡነ ባስልዮስ ሊቀጳጳስ፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የመንክር ኀይላ ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ።


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን።

ወጢን ስነ መዊዕስ ወፈጽሞ እምኃበ እግዚአብሔር።ዮሐንስ አፈወርቅ። እናንተ ሥራዉን ጀምሩ እግዚአብሔር ለፍጻሜው ሰራተኛ ሰው ያመጣል።

በዚች ምድር የሰው ልጆች የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት ብዙ እቅዶች ያቅዳሉ። እቅዳቸውን ከዳር ለማድረስ ደግሞ፡ ከፊት ለፊታቸው ብዙ እንደ አቀበት የከበደ ተራራ፡ የተደቀነ አስቸጋሪ መሰናክሎች ያጋጥማቸዋል። ሥራዎች ሲሰሩም እንቅፋቶችም አይታጡምና፡ በዚህም የተነሳ ያሰቡት ሃሣብ ብዙ ጌዜ እቅድ ከመሆን አልፎ፡ ለፍሬ የሚደርስበት ጌዜ እምብዛም አይታይም።  በእንቅፋቶችም የተነሳ ተስፋ ቆርጠዉ በሃሳባቸው አንድ እርምጃ ወደፊት ሳይራመዱ ድካማቸው ፍሬ ሳይሆን ዘወትር ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀርባቸዋል። ነገር ግን፡ ከዚህ ጎን ለጎን በተወሰኑት ደግሞ፡ የሃሳባቸውን ውጥን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ፡ የሚያጋጥቸውን ፈተናና መሰናክል በመቋቋም፡ ለፍሬ የበቁ ጥረታቸውን በውጤት የሚገልፁ አይጠፉም።  ለዚህም፡ በሮቸስተር ከተማ (ሲቲ) የምትኖሩ፡ በመንፈስ የተቃኛችሁ ክርስቲያኖች ሁሉ ለምሣሌ የምትጠቀሱ ናችሁ።  ክርስቶስ በፀጋው መርጦ በፍቅሩ ስቦ ወገኖቹ ያደረጋችሁ፡ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናን፡ የቅድስት ኪዳነ ምህረት ታቦት ከነበረበት ጠባብ እና በቁመት አጭር ቤት፡ ወደ ትልቅ የተሻለ ቤተክርስቲያን ለማሻገር በነበራችሁ የተቀደሰ ሃሣብ ላይ ተገኝቼ፡ አባታዊ ምክሬንና ቡራኬ እንደሰጠኋችሁ፡ የድሳቱ ስራም በጥሩ እንደሚጠናቀቅ፡ እናንተ ስራውን ጀምሩት እንጂ ለፍፃሜው ሰራተኛውን እግዚአብሔር ያመጣል፡ በማለት ተናግሬ ነበር።  አስታውሣለሁ ይህንን የተናገርኩት፡ የመልካም ሥራ ሁሉ ጀማሪና ፈፃሚ የሆነው ቸሩ አምላካችን፡ በጀመርነው ሥራ የእርሱ እርዳታ ሳይለየን፡ ይህንን የመሰለ ቤተክርስቲያን አድሰን እንድናይ ፈቃዱ እንደሚሆን ስለማምን ነው።  ዛሬም ቢሆን በረድኤት ያልተለየን እግዚአብሔር፡ ሃሣባችንን ስለባረከልን እያመሰገን፡ በዚህ የተቀደሰ አላማ የተሳተፋችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ሁሉ፡ እግዚአብሔር የጎደለውን ይምላላችሁ። ሃሣባችሁን ያሳካላችሁ። በእድሜ በፀጋ ይባርካችሁ።  

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አለማችንን ሁሉ ይባርክ፡ አሜን።

አቡነ ባስልዮስ ሊቀጳጳስ

የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የመንክር ኀይላ ቅ/ኪዳነ ምህረት ቤ/ክ የበላይ ጠባቂ።


የደብሩ አስተዳዳሪ መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን።

ገንዘብን ልናዉቅበት እንደሚገባ

ገንዘብ የሰዉ ልጆች ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ማንኛዉንም አይነት ፍላጎታቸውን ለማሳካትና ዕዉን ለማድረግ፡ የሚችሉበት አንዱ መሳሪያቸዉ ነዉ።  ስለሆነም ይህን እግዚአብሔር የሰጣቸውን ገንዘብ በስራ ላይ በማዋል፡ ለራሳቸዉና ለሃገራቸዉ፡ አንዲሁም ለወገኖቻችን የሚጠቅም ስራዎችን በመስራት፡ ገንዘብን በአግባቡ የሚጠቀሙበት ብዙዎች ሲሆኑ፡ በሌላ በኩል ደግሞ፡ አንዳዶች ገንዘብን ለጥፋት መንገድ በመጠቀም፡ እራሳቸውን ለችግር እና ለበሽታ እንዲሁም ለሃጢያት በመዳረግ፡ ከአምላካቸው ጋር ተጣልተዉበታል። Žገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ እንደሚባለው።Ž ሐብታሞችም ገንዘብ ስላላቸው ብቻ፡ ለነሱ ብቻ የቀና መንገድ አለ በማለት አይደለም።  እግዚአብሔር የሰጣቸውን ገንዘብ እንደጣዖት ሳያፈቅሩትና፡ የሃጢያት ማስፈፀሚያ ሳያደርጉት፡ ለፅድቅ ስራ በማዋል የተቸገሩትን በመደገፍ፡ የተራቡትን በማብላት፡ ለእግዚአብሔር ቤት አስራትን በማዉጣት፡ ህንፃ ቤተክርስቲያንን በመገንባት፡ እንዲሁም በማደስ፡ ገንዘባቸውን በአግባቡ ከመሩበት፡ የነፍስን ስንቅ ከሰነቁበት፡ የገነት መግቢያ ቁልፍን ከገዙበት፡ በሚያልፍ ገንዘብ የማያልፍ ገንዘብን ካፈሩበት፡ እዉነትም ለሰማያዊ ቤታቸው መንገድ አላቸው ለማለት የተነገረ አባባል ነዉ።  በሌላ በኩል Žገንዘብን መዉደድ የሃጢያት ሁሉ ስር ነዉ።Ž ያለው ሃዋረያዉ ቅ/ጳውሎስ፡ ለክርስቲያኖች ገንዘብ አያስፈልግም ማለቱ አይደለም።  ገንዘብን ከእግዚአብሔር በላይ ሳያደርጉ፡ ወንድማቸዉን ከማጥፋት፡ ሃይማኖት ከመካድ፡ በመጠጥ ሱስና በዝሙት ለመጠመድ፡ ገንዘብን የሚወዱና የሚናፍቁ መሆን እንደሌለባቸው ሲገልፅ ነዉ።

ገንዘብን ለአወቀበት የሕይወት የፅድቅ ምንጭ ናት። እነአብረሃም እንግዳ አሰናግደዉበታል። እነ ቅዱስ ዳዊት እነ ሰሎምን ቤተክርስቲያንን ሰረተውበታል። ያላወቁበት እነ ይሁዳ፡ ሐናንያም እና ሰጲራ፡ የሞት ገመድ ገዝተዉበታል። ዛሬም ከላይ በረዕሴ እንዳነሳሁት በእዚህ በሮቸስተር ከተማ (ሲቲ)፡ የሚኖሩ ህዝበ ክርስቲያኖች፡ እንዲሁም አጎራባች ከተሞች ለቤተክርስቲያናችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ፡ ዋጋቸውን በሰማይ ቸሩ ፈጣሪ ይክፈልልን፡ ከማለት ውጭ ምን ይባላል። ከሰሩት ሰማያዊ ስራ በመስራት፡ ገንዘባቸውን አውቀዉበታል። ስለዚህ በእዉነት ይህን አስተዋፅአችሁን፡ ለሃጢኣት ሳይሆን ለፅድቅ በማዋል፡ ገንዘባቸውን ለበረከት አውለውታል።  ስለዚህ በእውነት ይህንን ስራ በመስራታቸዉ፡ ዘወትር ቤተክርስቲያን በታሪክ ስታስታውሳቸዉ እና፡ በጸሎት ስታስባቸው፡ ከፊት ለፊት ብርሃን ሆኖ እነሱነታቸዉን ሲገልጽ ይኖራል " መልካሙን ስራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።" ማቴ ፭፡፲፮

መላከ ኃይል ቆሞስ አባ ወልደሩፋኤል ገ/ኢየሱስ

የደብሩ አስተዳዳሪ