ሰበካ ጉባኤ 

እግዚአብሔር ሆይ የሰጠኸንን ሰጠንህ።

በባህሪዉ ንፍገት የሌለበት፡ ቸርነት የባህሪይ ገንዘቡ የሆነ፡ እግዚአብሔር አምላክ የጥበብና የእውቀት ባለቤት እንደመሆኑ መጠን፡ ለሰው ልጆች ይጠቀሙበት ዘንድ፡ እንደፀጋቸው መጠን የተለያየ የእዉቀት ስጦታ ተሰጥቶአቸዋል።  የሰው ልጅም ከፈጣሪው የተቸረውን ጥበብ በመጠቀም፡ በምድር ላይ ይጠቅመኛል ብሎ የሚያስባቸውን ብዙ ቴክኖሎጂዎችን ፈብርኮ (ሰርቶ)፡ በስራ ላይ በማዋል ይጠቀምበታል።  በሰማይ ከሚበሩ ተንቀሳቃሽ ነገሮች አንስቶ፡ በምድር የሚታዩ ማንኛዉም ሰዉ ሰራሽ ስራዎችን ስንመለከት፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች እዉቀቱን የገለፀበት ጥበቡ እንደሆነ እንረዳለን። በመሆኑም የሰዉ ልጆች ይህን ያገኘዉን ፀጋ በመጠቀም፡ ያወቁትን በመያዝ፡ ያላወቁት ላይ በመድረስ፡ ብዙ ጥናቶችንና ምርምሮችን ያደርጋሉ።  ያልተረዱትን ለማወቅ ይጥራሉ።  በጸሎት ወደ ፈጣሪያቸዉ ያሳስባሉ።  የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፡ እንዳለው ጠቢቡ ሰለሞን፡ እንደ እግዚአብሔር ህግ በመጓዝ፡ በጥበባቸው ሳይመኩ ረዳታቸዉ እግዚአብሔርን በማድረግ፡ ብዙ አዳዲስ ግኝቶችን በማገኘት፡ ለራሳቸውና ለወገናቸው እንዲሁም ለሃገራቸው፡ አመርቂ ስራዎችን ሰርተዉ አልፈዋል።  እየሰሩም ያሉ አሉ።  

በሌላ በኩል ደግሞ፡ እዉቀታቸዉን ለጥፋት ያደረጉ፡ ችሎታቸዉን ከእግዚአብሔር በላይ በማድረግ እዉቀታቸውን ጣዖት የሆነባቸው፡ ከኔ በላይ ጥበበኛ ማን አለ የሚሉ፡ የዚህ ዓለም አስገኝና ፈጣሪ የሆነውን እግዘብሔርን ዘንግተው፡ አንድ ኃይል ብቻ አለ በማለት፡ የእግዚአብሔርን ስም እንዳይመሰክሩ በትዕቢት የታጀቡም ነበሩ።  አሁንም አይጠፉም። በመፀሓፍ ቅዱስ ዉስጥ እንደምናነበው፡ እግዚአብሔር ለብዙ አባቶቻችን እዉቀትንና ጥበብን ገልፆላቸው ሳለ፡ ብዙ ስራዎችን ሰርተው እያሉ፡ አኛ የማንጠቅም ባርያዎች የምድር ትቢያዎች አላዋቂዎች ነን በማለት፡ እራሳቸዉንና ዕዉቀታቸውን እንዲሁም ስልጣናቸውን ከፈጣሪያቸው በታች ሲያደርጉ፡ እንደ አርዮስ ያሉ፡ በዕዉቀታቸው ከመጠቀም ይልቅ፡ አምላካቸውን ክደውታል።  በመሆኑም፡ በዚህ ዘመን ላይ ያለን ክርስቲያኖች፡ በአለማዊ ዕዉቀት ዶክተር መሀንዲስ ሌላም ብንሆን፡ በዕዉቀታችን ለእግዚአብሔር ተገዥዎች መሆን አለብን። ሁላችንም ለእግዚአብሔር እናስፈልገዋለን እና፡ በስጋዊ ኑሮአችን ተሰልፈን በዕዉቀታችን ሰርተን ዕራሳችንንና ቤተሰባችንን ለመምራት ደፋ ቀና እንደምንል ሁሉ፡ በእግዚአብሔር ቤትም ያለንን ዕውቀት ማዋል አለብን።  መንፈሳዊ ምግብ እናገኝበታለን እና፡ መሃንዲስ በቤተክርስቲያን ግንባታ ላይ ፕላን በማውጣት፡ ለግንባታው ሂደት በሙያው ምክሮችና ክትትል በማድረግ፡ ሁሉም በዕውቀቱ በመሰለፍ ሰዓታችንና ጊዜአችንን በማመቻቸት፡ የልጅነት ግዴታችንን ለመወጣት፡ ዕውቀታችንን በእግዚአብሔር ቤት ማፍሰስ ይኖርብናል። ሐዋርያው ቅ/ጳዉሎስ Žስለራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም፡ ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፡Ž 1ኛ ቆሮ ፲፪፡፭ በማለት፡ መመካትን መጥላት።

ሁላችንም በአለማዊ ዕዉቀት ከሌሎች ከፍ ብንልም፡ በእግዚአብሔር ፊት ግን ሁላችንም እኩል መሆናችንን አዉቀን፡ ለቤተክርስቲያን ልማትና ግንባታ ያለንን ሁሉ በመስጠት፡ ዕዉቀታችንን ከእግዚአብሔር በታች ማድረግ አለብን።  ዛሬም በሮቸስተር ከተማ (ሲቲ) እና አጎራባች እስቴቶች፡ ምእመናን ህዝበ ክርስቲያን እና የሌላ እምነት ተከታዮችም፡ የሚቻላቸውን አድርገዉልናል።  ለዚህም ከፍተኛ ምስጋናችን ከልብ ነዉ።  ዕለት ዕለት የሚያሳስበኝ የቤተክርስቲያን ነገር ነው፡ እዳለዉ ቅ/ጳዉሎስ፡ የቤተክርስቲያን ችግር ተሰምቶቷቸውና አሳስቧቸዉ፡ ከቤተክርስቲያኗ ኮሚቴ ጋር በመሆን፡  ዕዉቀታቸውንና ገንዘባቸውን በእግዚአብሔር ቤት በማድረግ፡ የቤተክርስቲያኑ እድሳት እንዲጠናቀቅ፡ ሌት ከቀን በመድከም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።  "ነገር ግን የሚበልጠውን የፀጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ" እንዳለው ቅ/ጳውሎስ 1ኛ ቆሮ  ፲፪፡፫፫  ሁሉም የቤተክርስቲያኗ ልጆች በተሰጠው ፀጋና ዕዉቀት፡ ያለውን ሃብት፡ ደከመን ሰለቸን፡ ራበን ጠማን ሳይሉ፡ ባላቸው የእረፍት ጌዜና ከስራ ሰዓታቸዉም በመሰዋት፡ ለበለጠ ፀጋ ለእግዚአብሔር ቤት በማዋል ከመጀመሪያው ጀምሮ፡ እስከ ፍፃሜው ድረስ፡ ዕዉቀታቸውን ገንዘባቸውን ጉልበታቸዉን በማፍሰስ ከእግዚአብሔር ያገኙትን፡  ሃብታቸውን ለእግዚአብሔር ቤት በማዋል "እግዚአብሔር  ሆይ የሰጠኸንን ሰጠንህ" ከራሳችን አንዳችም ነገር የለንም፡ ሁሉም ያንተ ስላንተ ነው፡ እኛ የማንጠቅምህ ባሪያዎች ስንሆን እናገለግልህ ዘንድ አንተ መረጥከን በማለት ላደረጉት አስተዋፅኦ እናመሰግንሃለን።

         ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

         የቅድስት ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ

የቅድስት ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ አባላት