የልጅነት ጥምቀት (ማየገቦ) ይህንን ጥምቀት በማየ ገቦ ተጠምቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕፀነ ዮርዳኖስ ተወልደን ሥላሴ በኛ የሚያድሩበት እኛ ከሥላሴ ጋር የምንወሓድበት የክርስቶስ አካል ቤተሰብ የምንሆንበት አማናዊና መሰረታዊ የመዳን ጥምቀት ነው። ለመዳን ይህ የልጅነት ጥምቀት የግድ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያናችን ከሚፈጸሙት 7 ምስጢራት መካከል ለመዳን የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ለመወለድ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ለመግባት ምስጢረ ጥምቀት፣ ምስጢረ ሜሮን፣ ምስጢረ ቁርባን እሊህ 3ቱ የግድ መፈጸም አለባቸው። አንድ ሰው እሊህን 3ቱን ምስጢራት ካልፈጸመ ክርስቲያን ሊሆን የእግዚአብሔርም ልጅ ሆኖ ሊወለድ ወደእግዚአብሔርም መንግሥት ሊገባ አይችልም። ይኸንም ሲያስረዳ ጌታችን በወንጌል ምስጢረ ጥምቀትን ባስተማረበት አንቀጽ ‹‹ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን›› ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል (ማር 16፡16) ዳግመኛም (ዮሐ 3፡ 5) ‹‹ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ›› ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። እንዲሁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ‹‹ክርስቶስ ተወልደ ክርስቶስ ተጠምቀ ወለደነ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ›› ክርስቶስ ተወለደ ክርስቶስ ተጠመቀ እኛንም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ወለደን።